
መጋቢት 5 2015
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ይህ ጸሎት የተዘጋጀው የሚከተሉትን ነጥቦች ተመርኩዞ ነው፦
- የክርስትያን ዋናው ተግባሩ አንድ እግዚአብሔርን አምላክ ነው ብሎ ማመንና ማምለክ 2. የክርስትያን ተግባሩ በፍጹም ልብ ለእግዚአብሔር መታዘዝና ትእዛዙን መፈጸም
- አንድ ክርስትያን ለአምላኩ ፍቅሩን የሚገልጽበት ትእዛዙን በማክበር መሆኑን መጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል - ክርስትያን የአምላኩን ትእዛዝ ባፈረሰ ጊዜ ከአምላኩ ጋር የሚታረቅበት ዋነኛ መንገድ
ንስሐ በመግባት ማለት የሳተባቸውን የሕይወት ሂደቶች ለክርስቶስ በመናዘዝ ለጥቆም እራሱን ለንስሐ አባት በማሳየት በጸሎት በጾም በስግደት ሆኖ ከግድፈት ለመራቅ በመሞከር ነው - በዚህ ዓለም ላይ የሚከሰተው ማንኛውም ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወይም በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ነው ብሎ መቀበልና በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ለሥራ መነሳት የክርስቲያን እምነት ነው
- ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትታወቀው በእምነቷ በመሆኑና በሕገ ልቦናና በኦሪት (በብሉይ ኪዳንና) የአዲስ ኪዳን እምነት በአንድነት የሚገኝባት በዓለም ላይ ብቸኛ ሀገር በመሆኗ
- በዚህ የንስሐ ጸሎት ውስጥ የተጠቅሱት ክስተቶች ማንም ለመክሰስ ሳይሆን እንደ አገርና እንደ ቤተ ክርስቲያን እኛ የእዚህ ዘመን ትውልድ እንዲሁም የቀድሞ አባቶቻችን የሳትንባቸውን ነገሮች አምነን በክርስቶስ ፊት ለማቅረብ ነው
- በብዙዎች አመለካከት እንደ አገር አካሄዳችንን መሳት የጀመርነው በ16ተኛው ክፍለ ዘመን ከግራኝ አሕመድ መነሳት በፊት ከነበረው ትውልድ ጀምሮ ቢሆንም ባለፉት 70 አመታት ወዲህ ግን ነገሮች ተባብሰዋል ስለሆነም ይህ የንስሐ ጸሎት ሁሉንም በደሎች አያካትትም ስለዚህ ይህ ዝርዝር የተሟላ እንዲሆን የሌሎችንም ተሳትፎ ይፈልጋል
ኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 11
እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፥ ሕጉንም ሥርዓቱንም ፍርዱንም
ትእዛዙንም ሁልጊዜ ጠብቅ።
ኦሪት ዘፀዓት መዕራፍ 19
5 ፤ አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ
ሁሉ የተመረጠ ርስትትሆኑልኛላችሁ፤
ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 15፤ ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ።
የንስሐ ጸሎት
አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክሆይ፥ በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ትእዛዝህንና ሥርዓትህን ሕግህንም አልጠበቅንም።
ጌታ ሆይ፥ ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃልኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ፥ ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤
እኛ ባሪያዎችህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ ኢትዮጵያ ልጆች ሌሊትና ቀን የምንጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የኢትዮጵያን ልጆች ኃጢአት እንናዘዛለን፤ በድለናልና ማረን።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልባችንን ሰብረን አምላካችን መሆንህን አምነን ወደ ንስሐ ስንመጣ ይቅር እንደምትለን በሙሉ ልባችን አምነን ነው።
በግላችንም ሆነ በቤተክርስትያንም ደረጃ ሆነ በሀገር ደረጃ ለሰራናቸው ከአንተ ትእዛዝ ውጭ ለሆነው ሁሉ በሀገር አቀፍና በቤተ ክርስቲያን ደረጃ እንዲህ እንላለን።
አምላካችን ሆይ መሬት እየደበደብን ጦርነት እንዲነሳ ተመኝተን ግራኝ አሕመድ እንዲመጣና እስከ ዛሬ ድረስ ለአገራዊ ጥፋት ጦስ የሆነውን እንዲመጣ ምክንያት ሆነናልና ይቅር በለን
አምላካችን ሆይ ከዚያም ለ300 አመታት በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍለን አገራችንና ቤተ ክርስቲያንችንን በድለናልና ይቅር በለን
አምላካችን ሆይ በአጼ ቴዎድሮስ የተጀመረው አገራዊ የአንድነት ጥሪ ባለመቀበል ለጎጣችን በማድላት ለብዙ ደም መፋሰስ ምክንያት ሆነናልና ይቅር በለን
አምላካችን ሆይ በማወቅም ባለማወቅም በእውቀት ማነስም ከአገራችን ነባራዊ ትምህርት ጋር ሳይሄድ የአውሮፓውያንን ትምህርት እንደልብ እንዲገባ በመፍቀድ እስከዛሬ የቀጠለ የትውልድ ጥፋት እንዲመጣ አስተዋጾ አድርገናል
አምላካችን ሆይ አገራቸውን በቅንነትና በአርበኝነት ያግለገሉትን እንደ በላይ ዘለቀ አይነት ጀግኖች በአደባባይ ሰቅለናል የንጹህ ሰው ደም አፍሰናል።
አምላካችን ሆይ አንተ የቀባኸውን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን አዋርደን አምጸን በገዛ ፈቃዳችን እኛ ከሳሽ እኛ ዳኛ ሆነን ለሃገራቸው ለሃይማኖታቸው ምንም እንዳልሰሩ በሽምግልና ጊዜያቸው ገለናል። የንጹህ ሰው ደም አፍሰናል።
አምላካችን ሆይ ለሃገራቸው ለወገናቸው የሰሩትን 60 ታላላቅ መኳንንቶችና ሹማምንቶች በግፍ ያለፍርድ ገለናል አስገድለናል።የንጹሃን ደም አፍስሰናል።
አምላካችን ሆይ የመንፈሳዊ አባታችን ቅዱስነታቸው አባ ቴዎፍሎስን አሳልፈን ሰጥተን እንዲገደሉ ምክንያት ሆነናል። የቅዱስነታቸው ደም በቤተ ክርስትያንና በልጆቿ ላይ እስከዛሬ አለ።
አምላካችን ሆይ የቤተ ክርስትያን አባቶችና እኛ ልጆቻቸው ቤተክርስቲያን ስትደፈር ነጻነት ሲገፈፍ ደም በሜዳ ላይ ሲፈስ ዝምብለን ተመልክተናል።
አምላካችን ሆይ የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴና ሹማምንተቾቻቸውን የቅዱስነታቸው አቡነ ቴውፍሎስን አስከሬን የሚገባቸውን ክብር ሰጠን ግባተ መሬት ሥነ ሥርዓት አልፈጸምንም።
አምላካችን ሆይ ብጹዓን አባቶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና እኛ ልጆቻቸው ምእመናን ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆርዮስ በጤና ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክነታቸውን ሲለቁ በዝምታ በማለፋችን ለቤተክርስትያን መከፋፈል አስተዋጸኦ አድርገናል።
አምላካችን ሆይ አንተ የቀባኸውን ቅዱስነታቸውን አቡነ ጳውሎስን አዋርደናል፤ ሰድበናል፤ ገስፀናል እኛው ከሰን እኛው ፈርደንባቸዋል።
አምላካችን ሆይ በመላው ሥራችን የአንተን ትዕዛዝ ባለማክበራችን ዓመጸኞች ሆነን በቤተ ክርስቲያናችን መታዘዝ ቀርቶ ተከፋፍለናል። ዓላማችን አንተን ፈጣሪያችንን ከማምለክ ይልቅ ቤተ ክርስትያንን የገንዘብ ማግኛ ዘዴና መጠቀሚያ አድርገናል።
ባለፉት አምስት አመታት በአገሪቱ ላይ በዘር እየተለዩ ወገኖቻችን ሲታረዱ ድምጻችንን እንደሚገባን አላሰማንም በጸሎት አለመንም በጦርነት ብዙዎች ሲረግፉ ሕፃናትና ሴቶች ሲደፈሩ ከንፈር ከመምጠት ያለፈ ነገር አላደረግንም
ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን ብለን፤ ከኃጢአታችንም አልተመለስንም እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ አንተ እግዚአብሔር ፊት አልለመንም።
አሁንም፥ አምላካችን ሆይ፥ የባሪያዎችህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ጌታ ሆይ፥ ስለ ቅዱስ ስምህ ስትል ፊትህን አብራ።
አምላችን ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን አገር ተመልከት።
አቤቱ፥ ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ፥ አድምጥና አድርግ፤ ማዳን የእግዚአብሔር የአንተ ነውና፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው።
አምላካችን ሆይ ይህንን ንስሐ ተቀብለህ ልባችንን ወደ አንተ መልስልን። ፍቅርን ትሕትናን መከባበርን መስማማትን ትሰጠን ዘንድ እንማፀንሃለን።
አምላካችን ሆይ እንደ ጥንት አባቶቻችን ከአንተ ከአምላካችን ጋር የልብ ግኑኝነት ኖሮን እንደነሱ ተዓምር የምንሰራ ትውልድ አድርገን።
አምላካችን ሆይ በእኛ በኢትዮጵያኖች ላይ የሚያንዣብበውን ጥላቻ ጦርነት አለመተማመን ደም መፋሰስና ለሎችም ጥፋቶች ሁሉ በቸርነትህ በይቅርታህ አቁመው
አምላካችን ሆይ በዘር በጎሳ በኃይማኖት የተከፋፈልነውን ሁላችንንም አንድነትን ስጠን
አምላካችን ሆይ እንደ ያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ሁሉን ነገር በምስጋናያለምንም ማጉረምረም ተመስገን ብለን እንድንቀበል በእምነት አጠንክረን
አምላካችን ሆይ ተዓምራትህ በኛ ላይ ይፈፀም ዘንድ ልባችንን አንጻልን፤ እምነታችንን አጠንክርልን
እነሆ፥ እነተ ተቈጣህ እኛም ኃጢአት ሠራን፤ ስለዚህም ተሳሳትን። ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። ስምህንም የሚጠራ፥አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፥በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል።
አሁን ግን፥ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን።
አቤቱ፥ እጅግ አትቈጣ፥ ለዘላለምም ኃጢአትን አታስብ፤ እነሆ፥እባክህ፥ ተመልከት፥ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን።
አምላካችን ሆይ አገራችን ኢትዮጵያ የእናትህ የእመቤታችንየቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳን ሀገር ሰጥተሃታልና በእናትህ አማልጅነት በሀገራችን በኢትዮጵያ ፍቅርን በቤተ ክርስትያናችን ትህትናን መታዘዝን በትዳራችን ፍቅርንና መተሳሰብን በቤተሰባችን መዋደድንና መደማምጥን በልጆቻችን እግዚአብሔርን መፍራትን ለሁላችንም ለአንተ ለጌታችን መድኃኒታችን በፍጹም ልባችን መታዘዝን ስጠን።
የቃል ኪዳን ሕዝብህ የሆንነውን እኛን ወገኖችህን አድነን! ባርከንም ስምህን ለምንጠራ ለእኛ ለአገልጋዮችህ ድል መንሣትንና ኃይልን ስጠን የቃል ኪዳን ሕዝብህ ልጆች ነንና ጠብቀን በመስቀልህ ታዳጊነት እርዳን በመስቀልህ ተቤዥን
ስለባለሟልህ አብርሃም ስለወዳጅህ ይስሓቅ ስለመረጥኸው እስራኤልም ብለህ
አቤቱ ቃል ኪዳንህን አስብ ይቅርታህን ፈጥነህ ላክ የፈጠርኸን እኛን ማረን የወገኖችህን ኃጢአት አስተሥርይ የእጅህን ፍጥረቶች እኛን ማረን አቤቱ አታጥፋን ይህ በአንተ ዘንድ አይደረግ
ስለእናትህ ድንግል ማርያም ብለን ስለአጠመቀህ ዮሓንስና ስለቅዱሳንህ ኹሉ ብለህ ኹልጊዜ በመስቀልህ ታዳጊነት እርዳን አቤቱ በፊትህ አታሳፍረን
እመቤታችን እናታችን ሆይ ወደእኛ ተመልከቺ ለእኛ ለልጆችሽ ለምኚልን ከችግርና ከኅዘን ኹሉ አድኚን
አቤቱ ቀን ከእኛ ጋር ሌትም በመካከላችን ኹን አንተ ከእኛ አትለይ ከእኛ ጋር ኑር ረዳትም ኹነን
አትተወን አትተወን አትናቀንም የሰላም አምላክ ሆይ ተራዳን (3 ጊዜ)
እመቤታችን ሆይ እመቤታችን ሆይ ወደእኛ ተመልከቺ የልጅሽም ሰላም በእኛ ላይ አድሮ ይኑር (3 ጊዜ)
አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ማረን (3 ጊዜ)
እርሱን እናመልከው ዘንድ እኛን ለፈጠረ እግዚአብሔር ምስጋና ይገባል፡፡ አምላክን ለወለደች ለንግሥታችንና እናታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል፡፡ ኃይልና ጋሻ መድኃኒትም ለኾነን ለክርስቶስ መስቀል ምስጋና ይገባል፡፡
ይህን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በአንድ አምላክ ስም ፤በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማልጅነት፤ በቅዱሳን ሊቀ መላዕክት አማላጅነት፤ በቅዱሳን ሁሉ አማላጅነት፤ እንለምንሃለን።
ስማነ አምላክነ
አባታችን ሆይ
እመቤታችን ሆይ
ይህ የንሰሐ ጸሎት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በመስከረም 2010 ለመጀመሪያ ተዘጋጅቶ የጊዜውን አንገብጋቢ ሁኔታ በመመልከት እንደገና በመጋቢት 2015 ተሻሽሎ ቀርቧል