በአንድ ወቅት እጅግ ልባምና መልካም ወታደር ነበር። አንድ ቀን በወታደራዊ አገልግሎቱ ወቅት በወታደር ካምፕ ውስጥ አገልግሎቱን ጨርሶ ለመሄድ የሚሰናዳ ወታደር በሐዘን ተውጦ ተቀምጦ አገኘው። መልካሙም ወታደር ወደ እሱ ቀረበና ‹ምንድነው ችግሩ? ጊዜህን በሰላም በመፈፀም እንደማንኛውም ሰው ከመደሰት ይልቅ ራስህን በእጆችህ ላይ አድርገህ ለምን ታዝናለህ? እኔ አሁን ከቤቴ የመጣ ደብዳቤ ደረሰኝ ፣ ‘የወታደሩ መልስ ነበር። ’ እኔ ባልነበርኩበት ጊዜ ባለቤቴ ከሌላ ሰው ልጅ እንደወለደች ከደብዳቤው ተረዳሁኝ። ጭንቅላቱንም እየነቀነቀ ለጥቂት ጌዜ ዝም አለ። ከዛም ዝግ ባለ ድምጽ ፣ ሀዘን ቁጣ እና የተጎዳ መንፈስ በተደባለቀበት ሁኔታ፣ በእሷ ላይ የማደርገው ነገር እያሳሰበኝም እያስፈራኝም ነው። ለዚያም ነው ወደ ቤት መሄድ የማልፈልገው። መልካሙም ወታደር በዝግታ ጠየቀው ከቤት ከወጣህ ጀምሮ በመንገድ እዚህ ዝቅ ብሎ ያለው የጋለሞታ ቤት ውስጥ ስንት ጊዜ ሄድክ? ወታደሩም ዝም ብሎ ለማስታወስ በሚመስል መልኩ ካሰበ በኃላ ብዙ ጊዜ ሄጃለሁ ብሎ ተናዘዘ። አየህ አለው መልካሙ ወታደር አንተም መጠበቅ አልቻልክም። ለእሷስ ቀላል ነበር ብለው ታስባለህ? አንተ ችግር የለብህም ወንድ ነህ። ለእርሷ ግን ችግር ውስጥ ለመግባት አንድ ጊዜ በቂ ነው። ያደረከውን አስታውስ። ከእርሷ የበለጠ ስህተት ውስጥ ነህ። ይቅር በላት። ወደ ቤትም ሂድ ፣ ልጁንም እንደራስህ ተቀበል። ይህን ካደረግህ ሁሉም ነገር ደህና መልካም ይሆናል ብሎ መልካሙ ወታደር መክረው።
ከጥቂት ወራቶች በኋላ መልካሙ ወታደር የምስጋና ደብዳቤ ደረሰው። በደብዳቤውም ላይ ወታደሩ ወደ ቤቱ ሲቃረብ አባትና እናቱን ተቀበሉት። ባለቤቱም በፍርሃት እና በጭንቀት በሩ ላይ ቆማ ትጠብቀው ነበር። መልካሙም ወታደር ካናገረው ወዲህ እጅግ ሰላም ተሰምቶት ነበር። በደስታ ወላጆቹን ተቀበለ። ከዚያ በደስታ ወደ ሚስቱ ሄደ። ልጁንም ወስዶም አቀፈው ሳመውም። ሁሉም አብረው ወደ ቤት ገቡ። ከዚያ በኋላ ዘመዶቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን እየጎበኙ በመንደሩ ውስጥ ተመላለሱ። ፡፡ እናም በሄዱበት ሁሉ ሕፃኑን በእቅፉ ውስጥ ይዞት ይዞር ነበር። ሁሉም ነገር በጣም አስደሳች ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁሉም በአንድነት በሰላም በእርካታ ኖሩ። ወታደሩ በዚህ ደብዳቤ መልካሙንና ልባሙን ጓደኛውን ስለ ጥሩ ምክሩ እጅግ አመሰገነ። ምክሩም ጥሩ ብቻ ሳይሆን ጥበብም የተሞላበት እንደነበረ መካድ አይቻልም። በሰዎች መካከል መስማማትና ፍቅር እንዲኖር አንድ መሠረታዊና አስፈላጊ ሁኔታ ካለ እያንዳንዱ የራሱን ድክመት መገንዘብና ማየት ነው።
ማቴዎስ 7: 1-5
እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
ክርስቶስ በመካከላችን ነው
ለዘላለሙም ይሆናል
ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ
ሚያዚያ 1, 2013 (April 9, 2021)
ከምንጭ መስክ
ቨርጂኒያ