አቤቱ መልሰን ፊትህንም አብራ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሕዝቤ ሆይ ሕጌን አድምጡ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ:: መዝሙረ ዳዊት 77(78): 1

በዚህ መዝሙር ላይ ምንም እንኳን እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ ምድር የሚደንቁ ተአምራትን አድርጎ ቢያስወጣቸውም ከወጡም በኃላ ይህ ተአምራት በተለያየ መልክ ቢቀጥልም እስራኤል ግን እግዚአብሔርን አልሰማም:: መዝሙረ ዳዊት 77(78) ቁጥር  32 ላይ “ከዚህም ጋር  እንደገና በደሉ ተኣምራቱንም አላመኑም” ይላል:: ዛሬም እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ተኣምራትን አድርጏል ነገር ግን ንስሐ ግቡ የሚለውን ቃል አልሰማንም:: ይህም ተኣምራት በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ለውጥ እንደማያመጣ ማስረጃ ነው:: የሚያመጣው ለጥቂቱ ብቻ ነው:: ክርስቶስ ከፈወሳቸው ለምፃሞች ተመልሶ ያመሰገነው አንዱ ብቻ ነው::

ይህ አልሆን ቢል እግዚአብሔር መቅሰፍት እንደላከባቸው እና በዚህም ትንሽም ቢሆንም ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ አድርጏል:: መዝሙር 77:34 “በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ” ይህም ቢሆን ግን እውነተኛ መመለስ አለመሆኑን ሲያመለክት በቁጥር 36-37 ላይ “በአፋቸው ብቻ ወደዱት በአንደበታቸውም ዋሹበት ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም በቃል ኪዳኑም አልተማመኑበትም” ይላል::

ታዲያ ምን ይሻለናል? ተኣምሩም መቅሰፍቱም አልመለሰንም::

መፍትሔው ከማመን ይጀምራል:: በሚቀጥለው መዝሙር ማለት በ78(79) ቁጥር  9 ላይ እንዲህ ይላል “አምላካችን መድኃኒታችን ሆይ እርዳን ስለ ስምህ ክብር አቤቱ ታደገን ስለ ስምህም ኃጢአታችንን አስተስርይልን::” ይላል::

Help us, O God our Saviour, for the sake of the glory of Thy Name; O Lord, deliver us and be gracious unto our sins for Thy Name’s sake.

አንተ ካልረዳህን አልቻልንም ብሎ አምኖ መጀመር እጅግ ወሳኝ ነው:: በጣም የሚገርመውና ለዚህ ጽሁፍ አርዕስት የሆነው ግን የሚገኘው በቀጣዪ መዝሙር 79(80) ቁጥር 3 ላይ የሚገኘው ቃል ነው ይኸውም  “የሠራዊት አምላክ አቤቱ መልሰን ፊትህንም አብራ እኛም እንድናለን::”  

O Lord of hosts, make us to return and cause Thy face to shine, and we shall be saved.

አንተ ካልመልስከን በራሳችን አልቻልንምና ብለን ልንጠይቀው ይገባል:: ጌታ እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠ የሚያስደስተው ነገር የለም:: እርሱም መልካም ልጆቼ መዳን ፈልጋችሁ መልሰን ብላችሁኝ እኔ እንዴት እምቢ እላለሁ በማለት በቀጣዪ መዝሙረ ዳዊት 80(81) ቁጥር 10 ላይ እንዲህ ይላል “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና አፍህን አስፋ እሞላዋለሁም” ይህ ማለት እኔ የምነግራችሁን ስሙ ተቀበሉ ሲሆን ብዙ ጊዜ ግን ማድረግ የምንፈልገው እሱ የሚነግረንን ሳይሆን እንዲደረግ የምንፈልገው በምናባችን ያለውን ያው ለውጥ የማያመጣውን ነገር ነው:: በዚሁ በመዝሙር 80:11-14 ላይ”ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም እስራኤልም አላዳመጠኝም እንደልባቸው ሥራ ተውኃቸው በልባቸውም አሳብ ሄዱ:: ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኃቸው ነበር በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር” ይላል:: ጠላት የተባለው በሕይወታችንም ውስጥ ሆነ በአገር ደረጃ የሚያስቸግረን ነገር ሁሉ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል::

ታዲያ እንዴት ይሻለናል? መልሰን ብለን ፀለይን ልመልሳችሁ ብሎ ቢመጣ በእኛ መንገድ ካልሆነ ብለን አሻፈረን አልን:: የእኛ ልብ መከፈት በትንሹም ቢሆን እንደተጠበቀ ሆኖ በሚቀጥለው መዝሙር81(82) ቁጥር 1 ላይ ” እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል” የሚለው ቃል ስለ ቅዱሳን የተነገረ በመንግሥተ ሰማያት ያሉትም በበረኸ ሆነው የሚጸልዪት አባቶቻችንና እናቶቻችን ጸሎትና ምልጃ አድነን ማለት ብቻ ነው የቀረን:: ትንሽም ቢሆን ከእኛ ይጠበቃልና እንንቃ:: እግዚአብሔር ይርዳን::

በፈጣን ተራዲኢነቱ የሚታወቀው ቅዱስ መርቆሬዎስ ዛሬ ሰማዕትነት የተቀበለበት ዓመታዊ በዓሉ ነው::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለ እናትህ ድንግል ማርያምና ስለ ቅዱስ መርቆሬዎስ ብለህ ይቅር በለን አሜን

ክርስቶስ በመካከላችን ነው

ለዘላለሙም ይሆናል

ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ

ኅዳር 25, 2013 (December 4, 2020)

ከምንጭ መስክ

ቨርጂኒያ

Leave a comment