ቅዱሳን አባቶች የተለያዩ የመንፈሳዊ ሕይወት ገጽታዎችን ሁሉ በየዘመናቱ አስተናግደዋል፡፡ እናም የአይነ ልቦና መታወር ርዕሰ ጉዳይ የሰውን ልጅ ህመም እና ፈውስ በተመለከተ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት መካከል ስለሆነ እነርሱም ስለዚህ ረዕስ ብዙ ብለዋል። ቅዱስ ማርቆስ የአይነ ልቦናን ሁኔታ በሦስት መልኩ ያስቀምጠዋል እነርሱም ከተፈጥሮ ከፍ ያለ(ልዕለ ተፈጥሮአዊ) እና ከተፈጥሮ ጋር ተቃራኒ የሆነው(ኢተፈጥሮአዊ) እና ተፈጥሮአዊ ናቸው።
አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ጽድቅ እና መለኮታዊ ጥበቃ ማየት በተሳነው ጊዜ አይነ ልቦናው ከተፈጥሮ ጋር ተቃራኒ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው። አይነ ልቦናው በዚህ ኢተፈጥሮአዊ ሁኔታ ውስጥ የገባ ሰው ሌሎች ሰዎች ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንደሚያዩት ያምናል ስለዚህም በሌሎች ላይ ለአመፅ ይነሣሣል፡፡ በሌላ አገላለጽ ይህ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ግፊት የሚመጣው ሰው እግዚአብሔርን ሲተው እና በስሜት ህዋሳት በተፈጠረው ዓለም ሲባዝን ነው፡፡ ይህም ሰው ማንኛውም በዙሪያው ለሚፈጠረው መጥፎ ነገር ሁሉ ሌሎችን ይወቅሳል። የአንድ ሰው አይነ ልቦና ተፈጥሮአዊ ሲሆን በሌሎች ሕይወት ጣልቃ ገብቶ አይፈተፍትም እንደ ተፈጥሮው ይሠራል ፣ ግን አንድ መጥፎ ነገር ቢከሰት እራሱን እና የእርሱን መጥፎ ሀሳቦች እንደ ዋና ተጠያቂ ይቆጥራል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኃጢያቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ያውቃል እናም ለእግዚአብሔርም ይናዘዛል። አዳምንና ሔዋንን እንዳደረጉት በሌሎች ላይ ጥፋቱን ከመጫን ይልቅ ራሱን በመወንጀል ከዚህ ክፉ በሽታ ለመፈወስ ይታገላል። አንድ ሰው የሁሉም መንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን በሚቀበልበት ጊዜ የአንድ አይነ ልቦና በርቷል ማለት ነው የሚያከናውነውም ነገር ከተፈጥሮአዊ በላይ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አይነ ልቦናው ከእግዚአብሄር ጋር የተዋሃደ ሲሆን በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ደስ ይለዋል። አይነ ልቦናው ሲበራ እና ከእግዚአብሄር ጋር አንድነት ሲኖረው ቅርፅ አልባ እና ቅርፅ የሌለው ይሆናል ፣ ማለትም ፣ በጭንቅላት ውስጥ ከሚፈጠሩ መጥፎ ምስሎች ፣ ከቅዝቶች እና ከአጋንንት ሀሳቦች ሁሉ ይላቀቃል ማለት ነው። እሱ መልካም ሀሳቦች አሉት ስለሆነም ከማንኛውም ጭንቀት ነፃ መሆኑ ይሰማዋል። በመሆኑም እንደምንገነዘበው በእግዚአብሔር ፣ በሰው አጋሮቻችን ላይ እና በሌሎችም ነገሮች ላይ የሚመጡ መጥፎ ሐሳቦች የሚፈጠሩት የአይነ ልቦና መታወር ወይም መታመም ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ የአይነ ልቦናችን ሁኔታ መገንዘብ ለነፍስ ህመም እና ፈውስ እንዲሁም በአጠቃላይ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ ነው።
ክርስቶስ በመካከላችን ነው
ለዘላለሙም ይሆናል
ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ
ጥቅምት 13, 2013 (October 23, 2020)
ከምንጭ መስክ
ቨርጂኒያ