የልብን የአትክልት ስፍራ ለማሳደግና ለመንከባከብ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያን አበው ምክር እና በማስረጃ (እውቀት) ላይ የተመሠረተ የሥነ-ልቦና ሕክምና ቴክኒኮች (ኮግኒቲቭ ቴራፒ)

በአረም የተዋጠን መስክ አትክልተኞቹ ምን እንደሚተከሉ መሬቱን እንዴት እንደሚሰሩ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ችግኞቻቸውን በመንከባከብ መስኩን ባማሩ አበባዎች የተሞላ ማድረግ ይቻላሉ። በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥም ፣ ኃጢአተኞች ኃጢያተኛ ሀሳቦችንና እፍኝቶች በንቃት ቢጠብቁና ቢከታተሉ የኃጢያት ልምምዶችንም በጾም በጸሎት በስግደት ቢያስወግዱና በንስሓ ሕይወት ውስጥ ቢመላለሱ ጥሩ መዓዛ ያላቸውን አበባዎችን (እሴቶችን) አዳብረው ወደ ቅድስና ሊደርሱ ይችላሉ።  በማስረጃ(እውቀት) ላይ የተመሠረተ የሥነ-ልቦና (ኮግኒቲቭ) ሕክምና ውስጥ የሥነ ልቦና ችግር ያለባቸው ሰዎች እንክርዳድ የሆነውን የተዛባ አስተሳሰብን (በኮግኒቲቭ ቴራፒ) ልምምዶች በማስወገድ የተወሰነ የአእምሮ ሰላም ሊያገኙ ይችላሉ። የስነ-ልቦና ሕክምና (ኮግኒቲቭ ቴራፒ) ጥልቅ የሆኑና የተሳሳቱ ስሜቶችን እምነቶችን ለመለየት እና መልሶ ለመቀየር እንዳይቀጥሉም ለማድረግ በግልፅ የተቀመጡ እና በጥንቃቄ የተቀናጁ የግንዛቤ ቴክኒኮችን ይጠቀማል። እነዚህን ቴክኒኮች በእቅድና ዝርዝር ተጠቅሞ ማንነትን መልሶ መገንባት የሚቻልበት ሁኔታ አለ።

በቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በኤፌሶን 4 ላይ እንደተጠቀሰው አሮጌውን ሰው አስወግዶ አዲሱን ሰው ለመልበስ በአጠቃላይ በሕይወት ጎዳናችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ የአእምሮአችንና መንፈሳችን መታደስ የሚገኘው በቅዱሳት መጽሐፍት እና በቅዱሳት ወግ (ባህል) መመራት ፣ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መካፈልን የሚያካትትና በእግዚአብሔር ጸጋ በመደገፍ ነው፡፡ ከሥጋዊ ፍላጎቶች የመንፃት ሂደት ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ብርሃንን መቀበልን ፣ እና ክርስቶስን መምሰል በሚደረገው ጥረት የአንድ ሰው መሠረታዊ እምነቶች ወይም እቅዶችን በከፍተኛ ደረጃ ይለወጣል።  ይህ ሂደት ዘር ወደ መሬት እንደሚጣል ከዚያም እንደሚበቅል እና እንደሚያድግ ሁሉ ቀስ በቀስ የሚሆን ነው። ምንም እንኳን መንፈሳዊ አባቶች ሊተክሉ እና ሊያጠጡ ቢችሉም ፣ ሁልጊዜ እድገቱን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡

ለምእመናን ምሥጢረ ድኅነት እጅግ በጣም ሰፊ እና መለኮታዊ ስለሆነ ውስን ከሆነ የስነ-ልቦና ቴክኒኮች ጋር ሊነፃፀር እንደማይችል እንደ ፀሀይ ያህል ግልፅ ነው፡፡ የአእምሮ ጤንነትን ለማግኘት በሚያደረግ ጥረት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በተመለከተ ክርስቲያን ሕመምተኞች የአበውን ምክር ማስቀደም ይኖርባቸዋል። በመልካም ዕለታዊ መንፈሳዊ ትግልና ሀሳቦች ላይ ማተኮር መንፈሳዊ መጽሃፍቶችን ማንበብ እራሳቸውንና ሌሎችን እና ዓለምን የሚመለከቱበትን እይታ መቀየር ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል። የፀሀይ ሙቀት የዝናብ እርጥበት እና በአፈሩ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች አንድን ዘር ተክል ወደ መሆን እንደሚረዳው ሁሉ የአበው ምክርና ጥበብ ቀስ በቀስ የምእመናን ልብ ወደ ጽድቅ ፀሀይ እንዲዞርና የሕይወት ውኃ ምንጭ ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በተከታታይ ጽሑፎች ተጨባጭ የሆኑ መንፈሳዊ ልምምዶችን እናያለን።

ክርስቶስ በመካከላችን ነው
ለዘላለሙም ይሆናል

ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ
ነሐሴ 20, 2012 (Aug 26, 2020)
ከምንጭ መስክ
ቨርጂኒያ

Leave a comment