አበው የክርስትና እምነት እና የአኗኗር ዘይቤ አስተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ምእመናን የተማሩትን መሠረታዊ መንፈሳዊ ፅንሰ ሀሳቦችን በሕይወታቸው ውስጥ በተግባር ላይ ለማዋል በተከታታይ መለማመድ እንደሚያስፈልግ በሚገባ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ክርስቲያናዊ በጎ ምግባሮች (Virtues) እንደማንኛውም ነገር በየቀኑ ልምምድ ማድረግን የሚጠይቅና የሌሎችንም ድጋፍ የሚፈልግ ነው። ምእመናን ከቅዳሴ መገልገያ መጽሐፍት፣ ካህናቱ ከሚሰጥዋቸው ስብከቶች ፣ ወይንም በንስሀቸው ወቅት ከመንፈሳዊ አባቶች ከሚሰጣቸው ምክር ውስጥ የሚያገኙትን በየቀኑ እንዲያጠኑትና እንዲያሰላስሉት አበው ያበረታታሉ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው ምእመናን ወደ ሌሎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ተግባራታቸው ከመግባታቸው በፊት በቤት ውስጥ የፅዋ ማኅበራትን በማቋቋም በቤተክርስቲያን ውስጥ ያገኙትን ማንኛውንም ነገር መከለስ ተገቢ ነው ይላል። ቅዱስ ዮሐንስ አክሎም ምእመናን በበጎነትን ብቁ ለመሆን ለየት ያለ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስረግጦ ይናገራል። ለምሳሌ ምእመናኑን ስለማንኛውም ሰው የሚያናድድና የሚያፀይፍ ነገር ከመናገር እንዲቆጠቡ የሚያበረታታ ነገር ሲነግራቸው በቤተሰባቸው ውስጥ ይህ የሚያፀይፍ ነገር ከተከሰተ አንዱ ሌላውን እንዲያርመውና እንዲሁም ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ልምምድ ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችሏቸውን መንገዶች ላይ እንዲሠሩ ሀሳብ አቅርቧል። በጥቅሉ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤት በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ መልካም ስነምግባር የሚማሩበትና አስፈላጊ የሆነውን ዕውቀት ሊያገኙበት የሚችሉበት በጎ ማሠልጠኛ እንደሆነ ያስተምራል።
ሌላው የአበው ምክር በዕለት ተዕለት የምእመናን ሕይወት ውስጥ በጎነትን በማስረፅ ረገድ አንድ ሰው የሚረብሽ ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ውስጥ እራሱን ሲያገኝ ምን ማድረግ እንዳለበት በአእምሮ ውስጥ አስቀድሞ የመለማመድ ልምድን ማዳበር ነው። ለአባቶች ይህ ልምምድ በመዝሙር 118: 60 እራሴን አዘጋጀሁ እና ትዕዛዛትን ለመጠበቅ አልተቸገርኩም የሚለውን መሠረት ያደረገ ነው። እነርሱም ሲተነትኑት አስቀድሜ ሊገጥመኝ የሚችለውን መጥፎ አጋጣሚን እንዴት እንደምመልሰው ገምግሜያለሁ ስለዚህም ይህንን መከራ በክርስቶስ አልፌዋለሁ ይላሉ። ጥንታዊያኑ አበው እንዲህ አይነቱ ከዚህ በፊት የተደረገ ዝግጅት ሦስቱ ቅዱሳን ወጣቶች የባቢሎን እቶን ውስጥ በድፍረት ለመግባት እንደረዳቸው እና ሌሎችንም ቅዱሳን ሰማዕትነትን ለመጋፈጥ አስችሎዋቸዋል። አማኞችም በፈተና ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉትን አስቀድሞ በመመርመር በተመሳሳይ የፍርሃትን ወይም የቁጣ የማይጠቅም ስሜታዊ ስሜቶችን ከመጠን በላይ መቀነስ ይችላሉ።
ቅዱስ ዮሐንስ እንደሚጠቁመው ትግዕሥት የሌላቸው ወይም ብዙ ጊዜ ቁጣና ንዴት የሚያጠቃቸው ሰዎች ልክ እንደተቸገሩ ፣ እንደተበደሉ ወይም እንደተጎዱ በአይነ ሕሊናቸው በማሰብ ነገር ግን ቅዱሳን እንደሚያደርጉት ፣ ፍጹም በሆነ ትህትና እና በልብ ገርነት መመለስን ልምምድ ማድረግ አለባቸው። በተመሳሳይም አማኞች ወደ አንድ ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ወይም ከሚራገሙና ከሚያዋርዱ ሰዎች ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ራሳቸውን እንደተሰደቡና እንደተዋረዱ በአይነ ሕሊናቸው በማሰላሰል አጋጣሚውን በምስጋናና በሰላማዊ መንገድ እንዴት እንደሚያልፉ እንዲዘጋጁበት ይመክራል። ይህ ዘዴ አንድ ሰው ሊያስባቸው የሚችሉትን ገጠመኞች ግምቶች መጥፎ ስሜቶች እና ምላሾችን አስቀድሞ በአይነ ሕሊና በማሰላሰል እራስን ከመጠን በላይ ከሆነ ስሜታዋ ምላሽ መጠበቅ ያስችላል። በቀኑ መጀመሪያ ጠዋት ላይ በዚያ ቀን ይሆናሉ ተብሎ በሚገመቱ ጥቃቶችን በማሰብ ከክርስቶስ ትዕዛዛት ጋር በሚስማማ መንገድ ምላሽ ለመስጠት በአእምሮ ማቀድ መልካም እንደሆነ ሀሳብ ያቀርባል። የጠፋው ልጅ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ወደ ልቦናው በተመለሰ ጊዜ በአይነ ሕሊናው ወደ አባቱ ቤት ሲሄድ ለአባቱ ምን እንደሚለው በማየትና በማሰላሰል ወደ ግቡ እንዲደርስ ትልቅ ድጋፍ ሆኖታል።
ይህ የጥንት የአበው ልምምድም መልካም ሥነ ምግባርን ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በየትኛውም የበጎ ሥራ ጥረት ውስጥ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉትን ችግሮች እና መሰናክሎች አስቀድመው በማሰብ ለሚያበሳጭ ወይም ለሚያዋርዱ ድርጊቶች እራሳቸውን ካዘጋጁ በእውነተኛ ህይወት ውስጥ ክፉ ነገር ሲገጥማቸው የተረጋጋና በጥበብ የተሞላ መልስ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል። ይህ የአበው ልምምድ የአእምሮ ጭንቀት በሽተኞች የሚገጥማቸውን መሰናክሎችን ለመለየት ይጠቅማል። ይህውም የጭንቀት ህመምተኞች በአንድ በተወሰነ ውጥረት ውስጥ በረጋ መንፈስ ምላሽ ለመስጠት ምን ማድረግ እንዳለባቸው አስቀድመው እንዲያስቡ በማድረግ ሕክምናቸው የተሳካ እንዲሆን የስነ፟ልቦና ሐኪሞች ይጠቀሙበታል።
መልካም መንፈሳዊ በጎነትን ለማግኘት በየቀኑ መታገል ፣ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ስለመኖር ከሌሎች ጋር መነጋገር ፣ የራስን ፈቃድን ስለ መከልከልን እና ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች ክርስቲያናዊ ምላሽ ማሰላሰልን ልምምድ ማድረግ ቀላል በሆነ መልክ ልንለምዳቸው የምንችል ልምምዶች ናቸው። እነዚህ ልምምዶች የኃጢያት ሀሳቦችን የሚያነሳሱ ዋና እምነቶችን እና አመለካከቶችን ቀስ በቀስ ማስወገድ ይችላሉ። ከሁሉም በላይ ፣ እነዚህ ለጽድቅ የሚደረጉ ልምምዶች የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዛት በመለኮታዊ ጸጋ በመደገፍ ለመጠበቅና ለመፈጸም ይረዳል። ከሁሉም በፊት ግን ፊታችንን ማዞር ያለብን ወደ ጌታችን ነው። ከዚያም እርሱ እንደመራን የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም እንችላለን። ስንጠቀምም አሁንም እርሱን በፀሎት እየጠየቅን መሆን አለበት። አለበለዚያ ያዳነን የእኛ ጥበብ ነው ወደሚል ትዕቢት ይወስደናል። መጀመሪያችንም መጨረሻችንም እግዚአብሔር ነው።
ክርስቶስ በመካከላችን ነው
ለዘላለሙም ይሆናል።
ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ
ነሐሴ 21, 2012 (Aug 27, 2020)
ከምንጭ መስክ ቨርጂኒያ