ውስጣዊ ጠላታችን ማን ነው? ክፍል 2

Ego (የተጋነነ እራስን ከፍ የማድረግ ስሜት) ምንድን ነው?

ክፍል 2

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። 

የክርስቲያን አባቶች በሥነ-ጽሑፎቻቸው የመንፈሳዊው ጉዞ ግብ የሰውን ልጅ ወደ ሙሉ በሙሉ ወደ የተለየ ሕይወት መለወጥ እንደሆነ ይመሰክራሉ። ይህም ራስን ከፍ ማድረግን የገደለ እና በሌላ መልኩ ደግሞ ዳግም እንድንወለድ የሚያደርገን ነው። ኢጎአችንንስ እንግደል ሲባል ምን ማለት ነው? እንደገና የምንወለደውስ በምን አይነት መንገድ ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል? ጌታችን ሁላችንንም እንድንለወጥ ጠርቶናል። የጠፋብንን እውነተኛውን ማንነታችንንም ሊሰጠን ይፈልጋል። ደቀመዛሙርቱ ክርስቶስን ወደ ታቦር ተራራ አናት ሲመለከቱ አካሉ ወደ ብርሃን ሲቀየር እንዳዩ ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ይህ ራስ ወዳድነት በሽታ በእውነት ሊለወጥ ይችላል። ብዙ ቀደምት አባቶች በደብረ ታቦር የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራዊ ለውጥ በክርስቶስ አካል ላይ አለመሆኑን ይገልፃሉ። ምክንያቱም ክርስቶስ ሁሌም ብርሃን ስለሆነ ለውጡ በሐዋርያቱ ዐይኖች ላይ ብቻ እንደነበረ ያብራራሉ። በዚያን ቅጽበት ዐይኖቻቸው ተለወጡ ተከፈቱ። እናም ክርስቶስ ሁልጊዜም እንደነበረው ሁሉ አንጸባራቂና በብርሃን የተሞላውን ክርስቶስን ለማየት በቁ። በትህትናቸው ፣ ክርስቶስን በመከተል ፣ ይህንን እውነታ ለማየት ወደዚህ ተራራ አናት ተወሰዱ። እኛም እያንዳንዳችን ይህንን በረከት ልንቀበል እንችላለን። ተፈጥሮአችንም ሊቀየር ይችላል። ይህ መለወጥ እውነተኛ እድገታችን ነው፡፡ ይህ በክርስቶስ የተቀበልነው መንፈሳዊ ሕይወታችን እራሳችንን የተሻለ ማድረግ ፣ ብልህ የመሆን ፣ ብዙ ነገሮችን የማወቅ ፣ ብዙ ጓደኞችን የማፍራት ፣ በሌሎች ላይ ተፅኖን የማሳደርን ስልጣንን የመያዝን ፣ ገንዘብ የማፍራትን ፣ ጤንነት መከናነብን ፣ ጥሩ ስም የመጠቀምን ጉዳይ አይደለም። ዋናው ነገር  በልባችን ውስጥ ያለው ጉዳይ ብቻ ነው። ዋናው ነገር በዕለት ተዕለት መንፈሳዊ ልምምዶቻችን በልባችን መስክ ምንም ዓይነት ራስን ከፍ የማድረግ መጥፎ ዘር ሊኖር እንደይችል ማድረግ ነው። ምክንያቱም ፈተና በሚመጣበት ጊዜ የሕይወትን ጣዕም እና በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላልና። ጌታ ሁል ጊዜ ንቁ እንድንሆን እና ወደ እርሱ “ጠብቀን እና ወደ ፈተና አታግባን” በማለት እንድንፀልይ አስተምሮናል። በዚህም ጥበቃ አማካኝነት የልባችንን ሁኔታ በጣም በግልፅ ማየት እንችላለን። ቀላሉን መደበኛ የሆነውን ሕይወት በመከተል ፣ እራሳችንን ፣ መንፈሳችንን እና አዕምሯችንን ማንፃት እንችላለን። ከዚያ በኋላ ለመንፈስ ቅዱስ ወደኛ መምጣቱ በጣም ቀላል ነው። ልክ እንደ ቅዱስ ቁርባን ማለት ነው። በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ካህናት ከኅብስቱ እና ከወይኑ ጋር ሆነው ሕዝቡ ሁሉ ዝግጁ ሆነው ፀሎት ይደረጋል። ካህኑም ባለ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይመጣና ኅብስቱንና ወይኑን ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ይቀይራቸዋል። በተመሳሳይ መንገድ ፣ እኛም እራሳችንን ማንጻት እንችላለን ፣ መንፈስ ቅዱስም ይለውጠናል። እናም የዓለም መጻሕፍት ሁሉ መያዝ ያልቻላቸውን ብዙ ብዙ ተሞክሮዎችን ያመጣና ይሰጠናል።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ራስን ከፍ የማድረግን ስሜት የማጥፋት እና በእግዚአብሔር አዲስ ሕይወት መቀዳጀትን ያሳዩና ያስመሰከሩ ታላላቅ መንፈሳዊ አባቶች አሉ። በመንፈሳዊ ውጊያው አሸናፊ የሆነ ሰው ምልክቶች ምንድን ናቸው? በእውነቱ ራስን ከፍ ከማድረግ የወጣ አንድ ሰው ውስጥ የባህርይ መገለጫው ምን ይመስላል? ብለን ጠይቀን ከአባቶች መማር አለብን። ውጊያውን ያሸነፈ ሰው ምልክቱ እርሱ ሁል ጊዜ ለሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። በጭራሽ አይደክምም ወይም የድካም ስሜት አይሰማውም። እርሱ ሁሌም ደስታ አለው። እርሱ ሁልጊዜ ለመስጠት ዝግጁ ነው። የሚኖረው ለሌሎች ብቻ ነው። ሁሉንም ለማገልገል ዝግጁ ነው። ክፉ ኃጢአተኛውን ጨምሮ በማንም ላይ አይፈርድም። እንደ ልጅ ነው፣ ግን እንደ የንጉሥ ልጅ ነው። የንጉሥን ልጅ ማን ሊነካ ይችላል? እናት አንበሳ በአቅራቢያዋ መሆኗን ካወቀ የአንበሳን ግልገል ማን ሊነካ ይችላል? ውጊያውን ያሸነፈ ሰው በተኩላዎች መካከል እንደ አንድ ትንሽ ጠቦት ይመስላል ፣ ግን አይፈራም። ራሱን መሥዕዋት አድርጎ ያቀርባል። ሁሉንም ሰው በመቀበል ፣ ፍቅርን ፣ ማገልገልን  ያሳያል። ለሁሉም ሰው ይፀልያል። በእያንዳንዱ አፍታ ለመሞት ዝግጁ ነው። እናም በዚህ በወደቀ አለም ሕይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው። የፍቅር ምንጭ ስለሆነም እነዚህ የፍቅር ፍሬዎች ይታዩበታል። ራሱን ከፍ ከማድረግ የነፃ ሰውም እንዲሁ ነው። ይህ ነው በክርስቶስ መለውጥ ማለት። ኢጎ የሌለው ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ሰው ነው ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያም ነው።

ራስን ከፍ ከማድረግ በልጦ የሄደ መንፈሳዊ አባት ሰዎች ከፍተኛ አቅማቸውን እንዲያገኙ ማነሳሳት ብቻ ሳይሆን እርሱን ለማየት ለሚመጡት ሰዎች ስለ ራስ ወዳድነት አስከፊነት የመጨረሻውን ፈታኝ የሆነ ተሞክሮዎ ሰጥቶ ወደ እግዚአብሔር ይመራቸዋል። በእንደዚህ አይነቱ መንፈሳዊ አባት ፊት ሰይጣን ወዲያውኑ ይወጣል። አንድ የእግዚአብሔርን መንፈስ የተቀዳጀ ሰው ፣ ኢየሱስ በጎዳናዎች ላይ ሲራመድ የታዩትን ነገሮች ማድረግ ይችላል።  አጋንንት የያዛቸው ሰዎች ማነህ አንተ?  እዚህ የመጣህው ችግር ለማምጣት ነው ይሉ ነበር። አንዳንዶቹ በኢየሱስ ምክንያት ተሰናክለዋል ፣ ሌሎች ደግሞ እንዴት እንደሚገድሉት እያሰቡ ነበር ፣ ሌሎች ደግሞ በእሱ ላይ መጥፎ ነገሮችን ያሰቡ ነበር። ጌታ የሚናገረው ግን እነሱ ለሚናገሩት ሳይሆን ገና ለሚያስቡት ነገር ነበር። እንዲህ አይነቱ ብቃት በመንፈስ ቅዱስ በበቁ መንፈሳዊ አባቶች ውስጥም ይገኛል። ከዚህ አይነቱ አባት ማንም ሰው መደበቅ አይችልም።

በክርስቲያን ሥነ ጽሑፎች ውስጥ ፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ ጠላት ብዙውን ጊዜ አስገራሚ በሆኑት እንደ ሰይጣን ፣ ሉሲፈር ፣ ዲያብሎስ በሚባሉት ይታወቃል። ሰይጣን የሚባለው ዋናው አስተማሪ ነው። እናም ego ራስን ከፍ ማድረግ ሲኖር የሰይጣንን ጽንሰ-ሀሳብ የምንፈጽምበት መንገድ ነው፡፡ ራሳችንን ከፍ አድርገን ከሥነ ምግባር ውጭ ስንሆን ለእሱ ዕጣን ማጤስ ያህል ነው። እርሱም ያውቀዋልና ይህንን ሲያሸት ይመጣል። ከዚያም ከኢጎችን ጋር ጓደኝነት ይጀምራል። ከዚያ ከእኛ ጋር መገናኘት ይጀምራል። ሰይጣን በእኛ ላይ ለመሰልጠን ሥልጣን የለውም ሁልጊዜም ለመወሰን ምርጫው የእኛ ነው።

በዘመናዊው ምእራባዊውን ሥነ-ልቦና ሀሳቦች መንገድ ችግሮችን ለመቋቋም አንድ ሰው በመጀመሪያ ጠንካራ በራስ መተማመንን ፣ በራስ የመመራት ስሜትን ማዳበር እንዳለበት በተለምዶ ሲነገር ይስተዋላል፡፡ ይህ ማለት ግን ፕሬዝዳንት ለመሆን መጀመሪያ የማፊያ ዋና መሪ መሆን አለብኝ እንደ ማለት ነው። ወይም “እኔ በመጀመሪያ ከዲያቢሎስ ጋር እሠራለሁ። እኔ የፈለግኩትን ሁሉ እንዲሰጠኝ ነገር ግን ከእሱ የበለጠ ብልህ ስለሆንኩ ኃይሌን ለበጎነት እጠቀመዋለሁ እንደ ማለት ያህል ነው። ይህ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።  ልጆችን እንዲማሩ ፣ እንዲዘምሩ ፣ አትሌቲክስ እንዲማሩ ፣ ህይወታቸውን የሚመሩበት ኢኮኖሚያዊ መሠረት እንዲኖራቸው ማድረጉ ጥሩ ነው። ግን ስንት የሀብታሞች እና የልጆቻቸው ሕልሞች ተበትነው እንደቀሩ ይታያል።  መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ግንበኞች ግን ጌታ ያልባረከውን ግንብ ለመገንባት ጠንክረው ቢሠሩ እንዲሁ በከንቱ ይደክማሉ። ይህ ራስን ከፍ የማድረግ በሽታ የሃያኛው ክፍለ ዘመን አምላክ (ጣዖት) ነው። ይህ እንደ ዘመናዊው ሃይማኖት እየታየ ነው። ኢጎ ማለት “እኔ በመንፈስ ቅዱስ መኖር አላምንም።” መንፈስ ቅዱስ የለም ማለት ነው። ግን ይህ ውሸት ነው። መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ይመራል። እናም እርሱን የሚፈልጉት ፣ የሚያዩት ፣ በእርሱ ውስጥ የሚተነፍሱ ፣ በውስጡ የሚንቀሳቀሱ እርሱን የሚወዱ ፣ የተባረኩ ብፁዓን ናቸው።

ክርስቶስ “ፍጹም ሁኑ“ ብሏል። ጌታ ፍጹም ስለሆነ እኛም ፍጹም ልንሆን እንችላለን። ምክንያቱም ጌታ የእኛን ተፈጥሮ ተዋህዷልና። ስለዚህ እሱ ይህን ካደረገ እኛ ማድረግ እንችላለን ፤ ከእርሱ ጋር መሆንም እንችላለን። በዚህ ስጦታ ምክንያት ፍጹም ሊኮን ይቻላል።  ፍጹም ላለመሆንም ይቻላል ምክንያቱም ስጦታውን ላለመቀበል ፣ ፍቅርንም ለመከልከል ስልጣን አለንና። እኛ እምቢ ብለን ስንል ከዚያ ሌላ አምላክ ያስፈልገናል። ይህንን ድንቅ ስጦታ አንቀበልም ስንል ከዚያ ሌላ ፍልስፍና ያስፈልገናል።  አዲስ መጽሃፎችን እና አዳዲስ ፅንሰ ሀሳቦችን መፍጠርም አለብን። ከኢጎ ነፃ መሆን ይቻላል። መሆን መቻልም አለበት። አስፈላጊም ነው። ይህ ሊሆን ያልቻለበት ምክንያት ሰዎች ማድረግ እንደሚቻል ስለማያውቁ ነው። ይህን አጋጣሚ የማይፈልጉ በመሆኑ እና ይህ እድል እንዲፈጠርላቸው ስለማይፈቅዱ የገድ ሌላ ፅንሰ ሀሳብን ይፈጥራሉ። እነሱ ግን ውሸትን እንደሚናገሩ በውስጣቸው ያውቃሉ። ምን አይነት ዶክተር ነው ለታመመ ሰው “እነሆ ህመምህ የእኛ ተፈጥሮ አንድ አካል ነው ብሎ የሚለው። ከሕመማችን ጋር አብረን መኖር አለብን እንዴት ይባላል። ስለዚህ ጥፍሮቻችንን መቁረጥ አያስፈልገንም። ፊታችንን መታጠብ አያስፈልገንም። ምክንያቱም ነገ እንሞታለንና። ይህ ምን ዓይነት ትምህርት ነው? አዎ ፣ ከኢጎ ነፃ መሆን ይቻላል። ግን እሱ ምስጢር (mystery) ነው።

የኦርቶዶክስ ሥነ-ምግባር (ልምምድ) (Ascetic practices of Orthodoxy) ሥነ-ምግባራዊ ድክመቶቻችንን ለመግታት አስፈላጊነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። መንፈሳዊ እሴቶች (ፆም ፀሎት ስግደት መሬት ላይ መተኛት)/ Asceticism / መሄድ ለፈለግንበት ቦታ መድረሻ መንገድ ነው። ባቡሩ ሊሄድበት የሚችል የባቡር ሐዲድ ነው። ብዙ ሰዎች / Asceticism / ማለት የተወሰኑ መመሪያዎችን መከተል ማለት የሚመስለው ሰው አለ። ነገር ግን በእኛ ላይ የተደነገገ ሕግ አይደለም። በእግር ኳስ ውስጥ ፣ ለምሳሌ የጨዋታው ሕጎች ከባድ ሆነው አይደለም፣ ግን ጨዋታው በትክክል እንዲካሄድ ስለሚረዳ ነው። እነዚህ በመንፈዊ ሕይወት የምናደርጋቸው ልምምዶችም እንደዚሁ ናቸው። ቤተ ክርስቲያናችን የምትሰጠን የጾም ጊዚያቶች ፣ ልዩ ልዩ የፀሎት ጊዜያት እንደ ሚስጥራዊ መንገዶች ወይም መድረሻ መንገዶች ያገለግላሉ። እነዚህን ምስጢራዊ መንገዶች መለኮታዊ ቃል ኪዳኖች ፣መለኮታዊ ትዕዛዛት እንከተላለን። ከጠቅላላው መደበኛ ሕጎች ውጭ ፣ በመንፈሳዊ አባት እና ልጅ መካከል በሚደረግ ግንኙነት ውስጥ የሚሰጡ የግል ሕጎችም ወይም ልምምዶችም አሉ። በዋሻዎች ወይም በጫካ ውስጥ ወይም በበረሃ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ቅዱሳን አሉ። እነርሱም ተመልሰው ለመምጣት አቅደው አይደለም ወደዚያ የሚሄዱት ፣ ወደዚያ ሲሄዱ ለዘላለም ይሄዳሉ። እናም ጌታ በዚያን ጊዜ ይመራቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ ዋሻ ውስጥ ተደብቃችሁ ፀልዩ አላለም። ያለው ወደ ዓለም ሂዱ አስተምሩ ነው ያለው የሚለውን እየጠቀሱ ይህንን እንደ ስህተት ይመለከቱታል። መታወቅ ያለበት ግን ይህ በበረሀ በብሕታዊነት የሚከናወን የቅዱሳን ሕይወት ለሁሉም የተፈቀደ አይደለም። ብዙዎች ሞክረውት አልተፈቀደላችሁም እየተባሉ ወደ ዓለም የተመለሱ አሉ። የቻሉት ግን ገዳም ገብተው ስለ ሰው ዘር ስለ እንስሳቱ ስለ ወንዙ በአጠቃላይ ስለ ፍጡራን ሁሉ ይፀልያሉ።  ከመንፈሳዊ ተግባራት ትልቁና ከባዱ ደግሞ በንፁህ ሕሊና ሆኖ ፀሎት ማቅረብ ነው። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ሰዎች ወደ ገዳም ሲሄዱ መንፈሳዊ ምክር እየለገሱ ያፅናናሉ። ብዙዎቹ የምንጠቀምባቸው መንፈሳዊ አባባሎች የተገኙት ከበረሀ አባትና እናቶች ነው። ፀሎታቸውም ዓለምን ስለሚታደግ እኛ በዓለም የምኖረው በሚያስፈልጋቸው ልንደግፋቸው ያስፈልጋል። በዓለም ያለነው ደግሞ እንደተጠራንበት ቤተ ክርስቲያንን እናገለገላለን።

ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ምድረ በዳ ዲያቢሎስን ለመጋፈጥ ሄደ። ከአርባ ቀናት በኋላ እመለሳለሁ ብሎ በአእምሮው አላሰበም። ከዮርዳኖስ ወንዝ በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁ ተጠምቆ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። ከአንዳንድ ሰዎች እይታ አንፃር ፣ ጌታ ብቻውን የሆነበት ጊዜ እንደባከነ ይቆጥሩታል። ወደ ህዝቡ ሄዶ ምግብ አልሰጣቸውም ፣ አልባረካቸውም ፣ አልመራቸውም ፣ ሲሉ ጊዜውን እንዳጠፋ ይቆጥሩታል። እርሱ ግን ወደ ምድረ በዳ ሄዶ ዲያቢሎስን ፣ “ጓደኛዬ ፣ ተመልከት ፣ እስከዛሬ ድረስ በሰዎች ነፍስ ስትጫወት ነበር። በገነት በሔዋን ውስጥ የጀመርከውን አሁን ከእኔ ጋር ትጨርሰዋለህ። እኔ ብቻዬን እዚህ ነኝ። አልበላም። አልጠጣም። የሌሊቱ የምድረ በዳ አስከፊ ቅዝቃዜም በአጥንቶቼ ውስጥ ነው። ስለዚህም እሰቃያለሁ። ነገር ግን እኔ ወደዚህ ልጫወት አልመጣሁም። እናም አንተ ወደ እኔ መጥተህ ድንጋዮችን ወደ ዳቦ እንድለውጥ ነገርከኝ። እንድሰግድልህ ነገረኝ። አንተ? የሕዝቤን ስልጣን እሰጥህ ዘንድ? ማን እንደሆንክ አውቃለሁ። አንተም ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ። በዚያም ቅጽበት ዲያቢሎስ ለሁሉንም ነገር እጅ ሰጠ። ስለዚህ መንፈሳዊ ተጋድሎ ልምምዶች መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው። ለሁሉም ነገር በእያንዳንዱ ጊዜ ለመሞት ዝግጁ መሆን – ይህ በረሃ ነው ፣ የተጋድሎ መንፈሳዊ ሕይወት ይህ ነው። መንፈስ ቅዱስንም ያመጣል። ቤተ ክርስቲያንም የምትነግረንን ከተከተልን ጌታም ይመራናል። ራስንም ከፍ የማድረግ በሽታንም ከእግራችን በታች ያደረግልናል። አሜን ይሁን ይደረግልን።

ክርስቶስ በመካከላችን ነው
ለዘላለሙም ይሆናል።

ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ
ነሐሴ 18, 2012 (Aug 24, 2020)
ከምንጭ መስክ
ቨርጂኒያ

Leave a comment