ውስጣዊ ጠላታችን ማን ነው? ክፍል 1

Ego (የተጋነነ እራስን ከፍ የማድረግ ስሜት) ምንድን ነው?

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።  አሜን። 

የመጀመሪያውና ከመላእክት ሁሉ ከፍ ብሎ የተሾመው ሳጥናኤል (ሰይጣን) እይታውን ከእግዚአብሔር አንስቶ ትኩረቱን ወደራሱ ሲያዞር የመጀመሪያው እራስን ከፍ የማድረግ የዘር ፍሬን አስገኘ፡፡ መንፈሳዊ ዓይኖቹን ከቅድስት ሥላሴ እይታ ፣ ከጌታ እይታ አነሣ፡፡ ራሱንም ተመለከተና ስለራሱ ማሰብ ጀመረ፡፡ እርሱም ዙፋኔን በከፍተኛው ስፍራ አደርጋለሁ እንደ እግዚአብሔር መሆን እፈልጋለሁ አለ፡፡ በዚያች  ቅጽበት ራስን ከፍ የማድረግ ታሪክና ህልውናን ጀመረው፡፡ ይህንን እንዲመጣ ያደረገው እውነትን እምቢ በማለቱ ነው። ኢጎ ፍቅር ሲሞት ማለት ፊታችንን ከእግዚአብሔር ላይ ስናዞር የሚወጣ መጥፎ አበባ ነው፡፡ ፍቅርን በምንገድልበት ወይም በሚሞትበት ጊዜ ውጤቱ ጤናማ ያልሆነ የተዛባ የተጋነነ በራስ መተማመንና ራስን ከፍ የማድረግ ስሜት ማምጣት (Ego) ነው፡፡

እራስን ከፍ የማድረግ ስሜት (Ego) ባህሪው ምንድን ነው? በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥስ እንዴት ይገለጻል?

ትልቁ መገለጫው ምንም ነገር ማመን ያቅተናል፡፡  ኢጎ(Ego) የሚወለደው ሌሎችን በማናምንበት ጊዜ ነው፡፡ እኛ ትክክል ነን ስንል ሌሎችን አናምንም፡፡ ምክንያቱም ሁለት ነው፡፡ አንደኛ ዓይናችንን ከእግዚአብሄር ላይ ስናነሳ ወደ እራሳችን ውስን ክፉና እና ሥጋዊ አስተሳሰብ ላይ እንወድቃለን፡፡ ሁለተኛ ደህንነት እንዲሰማን ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠርም እንፈልጋለን፡፡ ያ በተራው ደግሞ የበለጠ ፍርሃት ያስከትላል። ሌሎችን እንፈራለን ፣ በዚህም ምክንያት ሌሎችን ለመቆጣጠር ጠመንጃ እንፈልጋለን፡፡ ይህም የተሳሳተ የአኗኗር መንገድ ስለሆነም ለራሳችን ዋስትና ለመስጠት የበለጠ እራሳችንን ከፍ ከፍ ወደ ማድረግ መንገድ እንሄዳለን። እናም ስለራሳችን ብቻ እናስባለን ፣ የሚታየንም ራሳችንን ከፍ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን እርስ በእርስ ከተያየን ፣ ከተማመንን ራስን ከፍ የማድረግ ፍላጎት ፣ ጤናማ ያልሆነ በራስ የመተማመን ስሜት እንዲኖረን ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡ ኢጎም (Ego) ምንም አይነት ዕድል አይኖረውም፡፡ ዐይኖቻችን እግዚአብሔር ላይ እስካሉ ድረስ አምላካችን ከሰዎች አቅም በላይ የሆኑ መንገዶች እንዳሉት ስለምናውቅ በውስጣችን እረፍትን የሚሰጥ እምነት ያድርብናል፡፡

ለዚህ ፍጹም ምሳሌ የሚሆነን በማቴዎስ ወንጌል ላይ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ነው። ይህ አገልጋይ ጠመንጃ አስፈልጎት ነበር፡፡ ጠመንጃ ማለት እራሳችንን ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ ማለት ነው፡፡ ጌታውን ባለማመኑ ምክንያት ወደ እራሱ ተመለከተ፡፡ ይሄም ፍርሃትን አመጣበት፡፡ እናም አገልጋዩ ለእርሱ መከላከያ ነው ብሎ ያሰበው መክሊቱን መቅበር ነው፡፡ መክሊቱንም ቀብሮ ግን እረፍት አላገኘም፡፡

ማቴዎስ 25: 24-25

አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡— ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ፡ አለ።

ኢጎ(Ego) ሲኖረንና ሲሰለጥንብን ከሰው ተለይቶ ማሰብንና ገለልተኝነታችንን እንፈልገዋለን፡፡ ትክክል ሆነም አልሆነም የሚያስደስተንና የሚያረካን የራሳችን አስተሳሰብ ብቻ ነው፡፡  እኛ ትክክለኛ ነን ብለን ስለምናምን እራሳችንን ከሁሉም በላይ እናስቀድማለን፡፡ የማንም እርዳታ ያስፈልገናል ብለንም አናምንም፡፡ እውነታው ግን ምንም እንኳን ትክክል ብናደርግምና ብንሆንም የሌላ ሰዎችን እይታ በማስተናገድ የተሻለ ግንዛቤን እናገኛለን፡፡ ስህተት እንደሠራንና እና የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልገን ግልፅ በሆነበት ጊዜ እንኳን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ ብቻችንን ለመወጣት በመሞከር እንሰቃያለን፡፡ ይህም በውስጣችን ያለውን ኩራት ከማመልከቱም በላይ እራሳችንን ከፍ ከፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለን በግልጽ ያሳያል፡፡ ድክመቶቻችንን ለመሸፈን እንፈልጋለን። አባታችን አዳም የተከለከለችውን ፍሬ ከበላ በኋላ በገነት ድክመቱን ለመሸፈን ሞክሯል፡፡

የክርስቲያን ሥነ ጽሑፎች እና ቀደምት አበው ራስን ከፍ አድርጎ የማየት ስሜት መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖር ለሚታገል ሰው ሁሉ እንደ ዋና ጠላት ወይም ተግዳሮት ያዩታል፡፡ ለምንድነው ይሄ ራስን ከፍ የማድረግ ስሜት እንደዚህ አስፈሪ ተቃዋሚና ጠላት ተደርጎ የሚቆጠረው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ኃይለኛ ጠላት አደገኛ የሚያደርገው በውስጣችን ያለ ጠላት ስለሆነ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት ሕግን አፋልሰው ለራሳቸው ጠላት እንደሆኑ ሁሉ እኛም እያንዳንዳችን ለራሳችን ጠላቶች ነን፡፡ በእርግጥ እባቡ ሔዋንን ሲያነጋግራት ወግድ ብላ ማስቀረት ትችል ነበር፡፡ እባቡም “ጌታ ዋሽቶሻል” ብሎ አላት፡፡ ግን እግዚአብሔርን ያለውን ሙሉ በሙሉ አምና ቢሆን ኖሮ እባቡን ማውራት ባልጀመረችም ነበር፡፡ አዳምም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጠ ፣ እናም ራስን ወደ መመልከቱ ሄድዋል፡፡  አዳምና ሔዋን ካለ እግዚአብሔር እራሳቸውን ከፍ የማድርግ መንፈሳቸው ተቀናጅቶ ሠርቷል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው ሁሉ እውነተኛው ጠላቱ እራስን ከፍ የማድረግ ስሜት (Ego) ነው፡፡ ጠላት የሆነበትም ምክንያት ፍቅርን የሚቃወም ስለሆነ ነው፡፡ ራሳችንን ስንመለከት ሌሎችን አንወድም፡፡ የሌላ የሆነውን ለራሳችን ለማድረግ ስንፈልግ ቃየን አቤልን እንደ ገደለው ሁሉ የወንድማችን ገዳይ እንሆናለን፡፡ ራሳችንን ለማርካት ስንፈልግ የሌላውን ነፃነት በመስዋትነት ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ከዚያም የእኛ ego ጌታና አምላካችን ይሆናል፡፡ ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ፈተና የለም፡፡ ይህ አካሄድ እንደሚያብረቀርቅ አልማዝ ሊመስለን ይችላል። እንደ ወርቅ አንጸባራቂ ብርሃን አለው፡፡ ነገር ግን የሚያበራ ነገር ሁሉ ወርቅ አይደለም፡፡ ራስን ከፍ የማድረግ መንፈስ ልክ ብርሃን እንደሌለው እሳት ነው፡፡ ሙቀት የሌለው እሳት ነው፡፡ ሕይወት በውስጡ የሌለው እሳት ነው፡፡ እራስን ከፍ የማድረግ ስሜት (Ego) ብዙ መልካም ጎኖች እና ብዙ አማራጮች ያሉት ይመስላል፡፡ ነገር ግን እራሳችንን የምንጠብቅበት ብቸኛ መንገድ አድርገን ነው የምናየው ፣ እያንዳንዱ ሰው ጠላታችን ነው ፣ እናም በጣም የምንጨነቅበት ነገር ቢኖር የራሳችን ማሸነፍና ድል መቀዳጀት ብቻ ነው፡፡

አንዳንዶቹ ታላላቅ መንፈሳዊ አባቶች አንድ ሰው ትክክለኛውን መንፈሳዊ መንገድ አካሄድ በትጋት በሚጀምርበት ጊዜ ከዚህ በፊት በጭራሽ ያላየውና ሊገምተው በማይችለው መንገድ እራስን ከፍ የማድረግ ስሜት (Ego) ጋር ፊት ለፊት ይጋጫል ይላሉ፡፡ ብዙ ቅዱሳን በዚህ አካሄድ ስላጋጠማቸው ነገር ሲናገሩ ፣ ይህ መንፈሳዊውን ሕይወት የማይፈልግ ፣ እግዚአብሔርን የማይፈልግ ፣ ግን በውስጣችን ያለ ዲያቢሎስያዊ ኃይል እንደሆነ አድርገው ሲገልጹት ፣ ይህ ረቂቅ ዲያቢሎስያዊ ኃይል ብርሃናችንን ለመግታትና ፣ ጽኑ አቋማችንን ለማዳከም የሚቻለውን ሁሉ ከማድረግ ወደኃላ አይልም ይላሉ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ክስተት ፣ በሰዎች ልብ ውስጥ ስላለው ስለዚህ ተጋድሎ በደንብ አድርጎ ጽፎልናል።  እርሱም እንዲህ ይላል-“የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዳላደርግ ፣ በእሱ ላይ ነገሮችን ለማድረግ ፣ ጸጋውን ላለመቀበል የሚናገር ሌላ ሕግ በውስጤ አለ፡፡ ወደ ድሮው ህይወቴ ሊመልሰኝ ይሞክራል፡፡ ጌታን ከመከተል እኔን ሊከለክለኝና ሊያርቀኝ ይፈልጋል፡፡” በዚህ ምክንያት ነው የሰው ልጅ ትልቁ ችግር በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ እንጂ ከእርሱ ውጭ ያልሆነው፡፡ ለዚህም ባለጋራ የሚረዱን መንፈሳዊ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡ መንፈሳዊ ሐኪሞች ያስፈልጉናል፡፡ ቀዶ ጥገና ያስፈልገናል፡፡ በልባችን ውስጥ ያለውን ይህን መጥፎ ነገር ቆርጦ የሚያወጣ እንፈልጋለን፡፡

በውስጣችን ያለው ይህ ጠላት የእኛ ስብዕና አይደለም፡፡ የእኛ ማንነት አይደለም። እኛ ላይ የሚመጣ ፈተና ብቻ ነው፡፡ ይህ የችግር ምንጭ የተገኘው ከተዘራው መጥፎ ዘር የመጣ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ሳናውቀው በዋጋ የማይተመን ስብዕናችንን ከስህተታችን ጋር እናዋህዳለን። ስብዕናችንን ከኃጢያታችን ጋር እናማታለን፡፡ በዚህም ምክንያት የተሳሳተ ግንዛቤ እንይዛለን። ምን እንደሆነ ለይተን አናውቀውም፡፡ ማን እንደሆንን የሚያሳይን ሰው እንፈልጋለን፡፡ ቢያንስ ያለንበትን የጨለማች መንገድ ማየት እንድንችል አይናችንን የሚከፍት ሰው እንፈልጋለን። አንድ ቅዱስ ሰው ለሠላሳ ዓመታት ይጸለይ የነበረው ፀሎት “ጨለማዬን አብራ ፣ ጨለማዬን አብራ::” እያለ ነበር፡፡ እርሱ ከሚተነፍሰው የበለጠ ይህንን ቃል ቀን ከሌት ይለው ነበር፡፡ ምክንያቱም ጨለማው ውስጥ እንዳለ በደንብ በመረዳቱ ነው፡፡ “እኔ የአለም ብርሃን ነኝ” ያለው ክርስቶስ ብቻ ከዚህ ጨለማ ውስጥ እንደሚያወጣው ስላመነ “ጨለማዬን አብራ” ስህተቶቼን አሳየኝ በማለት ድኅነትን አግኝቶበታል፡፡ በህይወታችን ውስጥ ማድረግ ከምንችለው ትልቁ ነገር እኛ በራሳችን የማንጠቅም ባሪያ መሆናችንን ማወቅ ነው፡፡ እኛ ጨለማ ውስጥ ነን፡፡ እኛ ያለ እግዚአብሔር ትቢያ ነን የሚለውን ማወቅና መረዳት ትልቅ ነገር ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ በመንፈሳዊው ሥነ ጽሑፍ ውስጥ እንደሚታየው ራስን ከፍ የማድረግ አባዜ መንፈሳዊ እድገታችንን ለመግታት የሚችል ተንኮለኛ ብልህ እና ሁሌም የሚለዋወጥ ባላጋራ ነው፡፡  ይህንን ውጊያ ለመታገል ምን አይነት እሴቶችንስ ማዳበር ያስፈልጋል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እራስን ሁልጊዜ ትክክል ማድረግ ኢጎን ለማስቀጠል አስፈላጊ ነው። አንዴ በዚህ መንገድ ላይ ከገባን ንስሐ ካልገባን በስተቀር አይተንው ወደማናውቀው ዝቅተት እንገባለን፡፡ ስለዚህ ይህንን ጠላታችንን ለማሸነፍ ኃጢያታችንን ተገንዝበን ንስሐ መግባት ነው፡፡ ይህም እኛ ማድረግ ከምንችለው ከፍተኛው ነገር ነው፡፡ ስለራሳችን እውነታውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችን ታላቁ ሶርያዊው ቅዱስ ይስሐቅ በጌታ ፊት ኃጢአቱን የሚቀበል ፣ የሚረዳ ፣ እርሱ የበላይ ነው ይላል ፡፡ እሱ በዓለም ሁሉ ከበለጠውና ከገዛው፣ ሰዎችን ሁሉ ከሚመግብ ፣ ተዓምራትን ከሚያደርግና ሙታንን ከሚያስነሳ ሰው ሁሉ የላቀ ነው ይላል፡፡  እንዲህ አይነቱ ሰው ትልቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በጌታ የተረጋጋ መንፈስ ስላለው ፈጽሞ ወደ ታች አይወድቅም። ጌታ በእንባው ፣ በንስሓው ፣ ስህተቱን እንደፈጸመ በማወቅና በማመን ጌታን ወደ ልቡ የሚጋብዝበት ቦታ አለው፡፡ ሁሉም ነገር ግልፅ ይሆንለታል፡፡ በብርሃንም ይሞላል፡፡ በብርሃንም ይመላለሳል፡፡ እሱ ኃጢያትን ለይቶ ለማወቅ ስላልፈራ መንፈሳዊ ሐኪም ፣ አስተማሪ ወይም አባት ይሆናል። “ይቅርታ ፣ የእኔ ጥፋት ነበር” ማለቱ ለእርሱ ችግር የለውም፡፡  ከሁሉም የዲያቢሎስ ፈተናና መሰናክሎች ለማምለጥ ይህ ቁልፍ ነው፡፡

ይህ ከላይ የተገለጽው የራስን ባሕርይ – በሐቀኝነት ፊት ለፊት ለመጋፈጥ የምናሳየው ፈቃደኛነት እንደ ትሕትና መግለጽ ትክክል አይደለም፡፡ ትሕትና የሚገኘው ውጤት ነው፡፡ “ጥበብ” ቢባል ይሻላል፡፡ እራሳችንን ትሑት ለማድረግ መንፈሳዊ ትግል እናደርጋለን። ግን ስህተቶቻችንን ለመለየት – ያ ከትሕትና ጋር ምንም አያገናኘውም፡፡ ስህተቶቻችንን ለመለየት ትሁት መሆን አያስፈልገንም። የሚያስፈልገው ስህተታችንን ማየት ብቻ ነው፡፡ እኛ ለአንድ ሰከንድ ከስህተቶቻችን ጋር እንዴት መኖር እንችላለን?— እንዴት ከችግሮቻችንና ከኃጢአቶቻችን ጋር እንዴት መኖር እንችላለን? “እኝ ኋጢያት ሰርተናል!” ማለት አለብን፡፡

ዶስቶይቭስኪ (Dostoyevsky) በወንጀል እና ቅጣት (Crime and punishment) በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ይህንን እጅግ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ ይገልፀዋል፡፡ ዋናው ገጸ-ባሕርይ ራስኮሊንኮቭ (Raskolnikov) አንድን ሰው ይገድላል፡፡ እናም እሱ ወዲያውኑ ያደረገውን ነገር ጥልቀቱን ይረዳል፡፡ ነገር ግን ይህንን በራሱ አላወቀውም ነበር፡፡ ድርጊቱን ያየች አንዲት ሶንያ የምትባል ሴተኛ አዳሪ ጥብቅ የሆኑ ጠንካራ ቃላቶች በመጠቀም  “ያደረግከውን ተመልከት” አለችው፡፡ እርሱንም ያደረገውን ለመናገር በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደ መሃል ከተማ ሂድ በማለት መራችው፡፡  እርሱም እንዳለችው በከተማው እምብርት ላይ ሆኖ የሠራውን ሁሉ ተናዘዘ። ይህንን ወንጀል ባይናዘዝ ኖሮ በሌላ መልኩ መኖር ስለማይችል ብዙ ወንጀሎችን ሊፈፅም እንደሚችል ይናገራል፡፡ እናም ቢያንስ ለሃያ ዓመት ወደ ከባድ እስር ቤት ለመሄድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ይቀበላል፡፡ በእዚያም የልቡ ድኅነትን ያስገኘለትን መራራ መድኃኒት ይቀምሳል። ብዙ ጊዜ ግን ኃጢያታችንን መቀበል ወይም እውቅና መስጠት ስለማንፈልግ በህይወታችን ውስጥ ችግሮችን እንጋብዛለን። ቁልፉም ይህ ነው፡፡ አንዳችን ለሌላችን ምን መስጠት እንችላለን? ወርቅ ፣ ገንዘብ ፣ ምኞት ፣ ምግብ? ረጅም ዕድሜ? በፍጹም ምንም መስጠት አንችልም። ነገር ግን ኃጢአታችንን ለይተን ማወቅ ብቻ ነው የሚያስፈልገን እና ወዲያውኑ አዲስ ዓለም ከፊታችን እናገኛለን፡፡

ክፍል 2 ይቀጥላል…….

ክርስቶስ በመካከላችን ነው
ለዘላለሙም ይሆናል

ዮናስ አሰፋ (አስበ ፃድቅ) ነኝ
ነሐሴ 14, 2012 (Aug 20, 2020)
ከምንጭ መስክ
ቨርጂኒያ

Leave a comment