ቅድስናና ቅንነት በከብቶች በረት

በምስራቃዊው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በቅዱስነት የሚታወቀው ቅዱስ ዮሐንስ ዘራሽያ እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቅድስናን ተቀዳጅቷል፡፡ በዚህ ዘመን ብዙ በረከት የተሰጠው ትውልድ ከቅዱስ ዮሐንስ ዘራሽያ ሕይወት ምን ይማራል? ወደ ቅድስና ላለመድረስ ምክንያት ብንዘረዝርም በዘመናት የኖሩት ቅዱሳን በፍርድ ቀን ይመሰክሩብናል፡፡ በተለይ ከቅዱስ ዮሐንስ ዘራሽያ የምንማረው አለመለገምን ነው፡፡ በማወቅም ባለማወቅም ዛሬ ብዙዎቻችን በአገራችን ላይ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በቤተሰቦቻችን ላይ ለግመናል፡፡  ለመለገም መናገር አያስፈልግም ውስጣዊ ነውና፡፡ መሰመር ያለበት ግን ልግምና ክፉን በክፉ መቃወም መሆኑና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል ትዕዛዝ የሚያፈርስ መሆኑን ነው፡፡  የቅዱሱን ታሪክ እነሆ

ቅዱስ ዮሐንስ ዘራሽያ ምስራቃዊው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በጣም ከታወቁ ቅዱሳን አንዱ ነው፡፡ የጦር እስረኛ እና ለቱርኩ የጦር ሰው አጊያ ባሪያ እንደመሆኑ ፣ በትህትናው ፣ በእምነትነቱ እና ርህራሄው በሙስሊም ጌታው እንኳን ታዋቂ እና የተከበረ ነበር ፡፡ የእርሱ ቅዱስ ቅርስ ባለበትም አስደናቂ ተአምር ይፈጸማል ፣ በአማላጅነቱ የሚያምኑት ቅዱሱ በተለይ የታመሙ ልጆችን እና በካንሰር ህመም የሚሠቃዩትን ይረዳል ይላሉ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ዘራሽያ በዩክሬን በ 1690 ገደማ ተወለደ ፡፡  ዕድሜው ሲደርስ ወደ ታላቁ የፒተር ሰራዊት ተመልምሎ በሩሲያ-ቱርክ ጦርነት (1710 – 1711) ውስጥ ተሳትፏል ፡፡ በውትድርና አገልግሎቱ ወቅት ፣ ከቤተሰቡ የተቀበለውን ጠንካራ የቤተክርስቲያን አስተምህሮና  ሃይማኖታዊ ትምህርቶች እንደ ሕይወቱ መመሪያ ይጠቀም ነበር ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ተማርኮ እስረኛ ሆኖ ተይዞ ለቱርክ ፈረሰኞች አለቃ አጊያ በባርነት ተሸጠ፡፡

እንደማንኛውም የተያዙ ክርስቲያን ወታደሮች ሁሉ ቅዱስ ዮሐንስ ማስፈራራት ፣ ማሰቃየት ፣ ወደ ሙስሊም እምነት ለመለወጥ በሁሉም መንገዶች ተጠቅመዋል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እስልምናን ለመቀበል አሻፈረኝ በማለቱ ቱርኮች ቃፊር ማለትም ኢአማኒ “የማያምነው” ብለው በመጥራት አዋርደው ስቃይ ያደርሱበት ነበር ፣ ዮሐንስ ለዚህ ኢ-ሰብአዊ ያልሆነ አያያዝና ፣ ድብደባ በጽናት የሚቋቋም ቆራጥ አቋም ነበረው ፡፡ ዮሐንስም ትገለኛለህ እንጂ ጌታዬን ክጄ እስላም አልሆንም፡፡ ነገር ግን ከተውከኝ በሌላው ነገ ሁሉ በደንብ አገለግላለሁ እያለ ለአጊያ ይነገረው ነበር፡፡

ነገር ግን ጊዜው እያለፈ ሲሄድ ፣ የቅዱሱን እምነት ፣ ትህትና እና ትጋት ፣ የተረዱት መቀለጃ ማድረጋቸውን አቆሙ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በጌታው እና በቤተሰቡ ክብርን ማግኘት ጀመረ ፡፡ የአሳዳሪውንም ፈረሶች እየተንከባከበ እዚያው በክፈፎቹ(በረት) ውስጥ ይኖር ነበር፡፡  አብረው ያሉት ሌሎች ባሪያዎች ለሥራው ባለው ቀናዒነት ያፌዙበት ነበር ፣ ነገር ግን አምላካዊ ፍርሃት ያለው ሰው ስለሆነ ፌዛቸውን ከምንም ባለመቁጠር እንዲያውም እድል ሲያገኝ በሥራቸውም ይረዳቸዋል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለማፅናናትም ይሞክራል፡፡ ቅን ልቦ ስለነበረውም የአሳዳሪውን የአጊያን ፍቅር እና እምነትን አግኝቷል ፡፡ አጊያም ከባርነቱ ነጻ ወጥቶ አንድ ክፍል ውስጥ በቤቱ እንዲቀመጥ ጠየቀው፡፡  እርሱ ግን “ጌታዬ ጌታ ነው ፣ ከእኔም በላይ ማንም የለም ፡፡ በባዕድ አገር እንደ ባርያ እንድኖር አስቀድሞ ወሰነልኝ ፡፡ ለእኔ መዳን ይህ ሊሆን ይገባል”  ሲል በበረት ውስጥ የጌታውን በበረት መወለድ እያሰበ ለመኖር ወሰነ፡፡

ዮሐንስ ቀኑን ሲሠራና ሲፀልይ ጾምንም ባለማስታጎል ይውላል ፡፡ ሲመሽ ሌሊቱን በሙሉ ይጸልያል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋሻ ቤተክርስቲያን (በድብቅ) ይሄድ ነበር ፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ ቅዱስ ቁርባንን ይቀበላል፡፡

ለኖረባት አጭር እድሜ ለሰው ልጆች ፣ እንስሳት እና በተፈጥሮ ውስጥ ላሉ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ፍቅር እና ርህራሄ ያሳይ ነበር፡፡ በመንገድም ላይ ሲሄድ እጁን በመሰቀለኛ አጣፍቶ ደረቱ ላይ በማድርግ “ቅዱስ እግዚአብሄር” የሚለውን ቃል እየደጋገመ ይናገር ነበር፡፡ ያያቸውን ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ሰላምታ እያቀረበላቸው የእግዚአብሔር ምህረትን እና ፍቅርን ይመኝላቸው ነበር፡፡

በአሳዳሪው በአጊያ ቤት ውስጥ ሁሉ ነገር በበረከት ተሞላ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሩሲያው አጊያ ቤት ከመጣ ጀምሮ ያለማቋረጥ ጤናማ እንስሳት ቁጥር በመጨመሩ ለጌታው ብልጽግናን አመጣለት፡፡ ታዛዥነቱ ፣ ለሰዎች ያለው አክብሮት እና ከሁሉም ሰው ጋር ተስማምቶ መኖር አጊያን በጣም አስደስቶታል ፡፡ ብዙም ሳይቆይ አጊያ ሀብታም ሆነ በከተማ ውስጥ በጣም ተደማጭ ከሆኑት ሰዎች አንዱ ሆነ፡፡ እርሱምይህ ሁሉ የሆነው በቤቱ ውስጥ በሚኖረው በቅዱስ ሰው እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡

ሀብታም ስለ ሆነ ሐጅ ለመሳለምም ወሰነ ፡፡ በዚህ ጉዞ ወቅት ባለቤቱ ለዘመዶቹ እና ለወዳጆቹ በቤትዋ ውስጥ የእራት ግብዣ አድርጋ ነበር ፡፡ የጌታው ተወዳጅ ምግብ ማንታ (እንደ ሬቪዬሊ ያለ የቱርክ ምግብ) በማቅረብ ላይ እያለ በጠረጴዛው ላይ ለሚያስተናግደው ለዮሐንስ እንዲህ አለችው: – “ጌታህ ይህን ማንታ ምግብ መብላት ቢችል እንዴት ይደሰታል?  ዮሐንስም ምግቡን ወደ መካ ለመላክ እንደሚችል ቃል እየገባ ይህን ምግብ በሰሀን እንድትሰጠው ጠየቃት ፡፡ ሁሉም ሰው ሳቀ ፣ የዮሐንስን ጥያቄ ግን ተቀበለችው ፣ እሱ ራሱ ይበላዋል ወይም ለድሆች ይሰጠዋል ስትል እንዲሰጠው አዘዘች።

ዮሐንስም ሰሀኑን ወስዶ ጸሎት ሲያደርግ ዐይኑ እያየየ ሰሀኑ ተሰወረ፡፡  አጊያም ከሐጅ ተመልሶ ሲመጣ በእሱ ላይ ስለተፈጸመው ተአምር ነገራቸው፡፡ በመካ ውስጥ እያለሁ በተቆለፈ ክፍሉ ውስጥ ትኩስ ማፍታ እንዳገኘና ሰሀኑም ላይ በቤቱ ሁሉ ላይ እንደሚታየው በእያንዳንዱ ሳህን ላይ የእርሱ ስም የተጻፈበት መሆኑን ተናገረ፡፡

የዚህ ተዓምር ዜና በፍጥነት ተሰራጨ ፣ እናም ሁሉም ሰው ፣ ሙስሊሞችም እንኳን ሳይቀሩ ፣ ዮሐንስን “Wali” ዋሊ- “ቅዱስ” ብለው መጥራት ጀመሩ፡፡ ሆኖም ፣ ዮሐንስ አኗኗሩን አልለወጠም ፣ እናም ሁልጊዜ ሥራውን ጠንክሮ በመስራት እና በመጸለይ ጊዜውን አሳለፈ። ከመሞቱ በፊት በጠና ታመመ፡፡ እናም ለመቆም ችሎታ ስላልነበረው ቅዱስ ቁርባን እንዲያቀብሉት ቄሱን ጠየቀ ፡፡ ካህኑ በይፋ ወደ ሙስሊም ቤት ለመሄድ ፈርተው ቅዱስ ቁርባኑን  ፖም ውስጥ ደበቀው በማምጣት አቆረቡት፡፡ ቅዱስ ቁርባንን ከተቀበለ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰኔ 9 ቀን ሩሲያው ዮሐንስ እ.ኤ.አ. ሰኔ 9 ቀን 1730 አረፈ ፡፡

ሰላም ለሁላችን
ዮናስ አሰፋ (አሰበ ፃድቅ) ነኝ
ሐምሌ 24, 2012
ከምንጭ መስክ
ቨርጂኒያ

Leave a comment